You are here: HomeOpinions“የመብት ይከበርልኝ!” እንቅስቃሴዎችን  ቤተክርስቲያን እንዴት ትያቸው?

“የመብት ይከበርልኝ!” እንቅስቃሴዎችን  ቤተክርስቲያን እንዴት ትያቸው?

Written by  Wednesday, 08 July 2015 00:00

በቅርቡ የአሜርካን ከፍተኛው የፌድራል ፍርድ ቤት የተመሳሳይ ፆታን ጋብቻ አስመልክቶ ባወጣው አዋጅና የተጋረጠበትን ተቃውሞ የሚዲያና የማሕበረሰብ ድረገጾች ሲያሰሙንና ሲያስነቡብን ሰንበተዋል፡፡ የአዋጁን መውጣት ተከትሎ የአዋጁን መውጣት ሲጠባበቁ የነበሩ ሰዶማዊያን (ቀላጮች ፣ ወንደቃዎችና ጾታ የቀየሩ ሰዎች) የጋብቻ ሰርተፍኬት ና የጋብቻ ፈቃድ ለመውሰድ በተለያዬ ፍርድ ቤቶችና አብያተክርስቲያናት የአጋቡኝ ጥያቄቸውን ሲያሰሙ እንደነበር አንደ ብሎምበርግ ያሉ ታላላቅ ጣቢያዎች አስደምጠዋል፡፡

 

አብዛኛው የወንጌላዊያን አማኞች በውሳኔው ላይ ለዘብተኛ አቋም ና መለሳለስ እንደታየባቸው የክርስቲያን ሚዲያ ኔት ዎርክ ዘግቧል፡፡ አነጋጋሪ የሆነውን የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ፤ ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ባያገኝም ፣ በማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ የሚያመጣው የሞራልና የመስተጋብር ተጽዕኖ  ከፍተኛ እንደሆነ የማሕበረስብ ሳይንስ ተመራማሪዎች ምስክርነታቸውን የሰጡበት ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ደጋፊዎቹና በዚሁ ልክፍት ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች መብታቸውን ከማስከበር አልፈው ተጽዕኗቸውን በሚኖሩበት ማህበረሰብ ፣ በተለይም በክርሰቲያኑ ሕብረተሰብ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ፣ አመለካከትና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ አሉታዊ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡

 

የምዕራቡ ዓለም አብያተክርስቲያናት እየቀረበላቸው ያለውን የአጋቡን ጥያቄ በአንዳድ ለዘብተኛ አቋም ባላቸው ቤተክርስቲያናት ውስጥ ተቀባይነት ያግኝ እንጂ አብላጫ በሚባሉት ዘንድ ጆሮ ያላገኝ ወደ ፊትም የማያገኝ ጥያቄ ነው፡፡ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችም ለዚሁ እኩይ ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ በመብት ተሟጋቾች ዘንድ የመብት ጥሰት ክስ አምጥቶባቿል፡፡

 

ወደ ኢትዮጲያ ነባራዊ ሁኔታ ስንመጣ ተመሳሳይ የሆነ የሰዶማዊያኑ “የመብት ይከበርልኝ!” እንቅስቃሴዎች  ከፍተኛ በሆነ በውጭ ሃገር መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ና የምዕራብ ሃገራት ነዋሪ በሆኑ ሰዶማዋዊያን  ትውለደ ኢትዮጲያዊያን   የሚታገዝ እንቅስቃሴ አንደሆነ የሃገር ውስጥ ጋዜጦች የዘገቡት ሃቅ ነው፡፡ በማሕበረሰብ ድረገጾች ላይ ይህንኑ ሰንካላ ሃሳብ የሚያራምዱ ስም- ኢትዮጲያዊ የሆኑ የግብረሰዶማዊያን ድጋፍና መብት አራማጅ የኢንተርኔት የመረጃ ገጾች ተበራክተዋል፡፡

 

የቤተክርስቲያን ፈተና በተለይም ይህንን መብት እንደ ሰብዓዊ መብት በተቀበሉ ሃገራት እጅግ የበረታ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ይህን መሰል ግልጽ ስጋት  ይጋረጥባት እንጅ ወደ ጥቃት የተሸጋገረና የመብት አክብሪ ጥቃት የደረሳባት አይመስለኝም፡፡ አስቀድሞ መጠንቀቅ ፤ ሊመጣ ያለውን ስጋት አስቀድሞ መለየት ሊደርስ የሚቸለውን ከፍተኛ  የመብት ጥያቄ ከወዲሁ እድንመክት ያስችለናል፡፡ ከዚሁም ጋር በተያያዘ አምስት ምልከታዎቼን  አንደ ማሰላሰያና የጸሎት አርዕሰት አድርጌ አቀርባለሁ፡፡

 

1. ቤተክርስቲያን የራስዋ የሆነ (ግላዊ - ከተገኘችበት ስፍራ ባህልና ትውፊት ተቃርኖኣዊ) ባሕል አላት

ቅድስት ቤተክርስቲያን መሰረቷ ፣ ባህሏ፣ እሰይቶቸና የትምህርቷ ምንጭ እግዚአብሔር በመሆኑ ምድራዊ መንግስቶችና ሰዋዊ ሥርወ-መንግስት በሚፈልገው አቅጣጫ ልትጓዝ አትችልም ፤ ይህም የባህል ግጭትና ተቃርኖ እየፈጠረ የሚሄድ ጤናማ የቤተክርስቲያን አቋም ማሳያ አጋጣሚ ነው፡፡  የቤተክርስቲያን ተግዳሮቶች በድህረ ዘመናዊነት ዘመን የሚያነጣጥሩት መሰረታዊ ወይም አበይት የቤተክርስቲያን እሰይቶች ላይ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

 

2. የክርስትናን መሰረታዊ ትምህርት ያለተቀበለ ማሕበረሰብ የክርስትናን እሰይቶች እንዲያከብር መጠበቅ የለብንም

ዘመንተኛ አስተሳሰቦችንና ፍልስፍና መር በመሆነው የድህረ ዘመናዊው ዓለም ፤ እውነት በንጽጽር ከመቅረቧም በላይ እውነት በግለሰብ ደረጃም ብትሆን እንኳን ግዜያዊና ዘሌቄታ የሌላት ነገር ናት፡፡ ለአንድ ሕበረተሰብ ክርስትና የእውነትና እውነተኛ የሆነው ጌታ ትምህረት ያለበት አስተሳሰብ መሆኑን ማስተማር የቤተክርስቲያን ሃላፊነት ነው ፤ ከዚህ ውጭ ቤተክርስቲያን የትኛውንም ጉልበት፣ ስርዓት ወይም መንግስታዊ መዋቅሮችን ተጠቅማ መጫን ተልዕኮዋ አለመሆኑን ልናጤን ይገባናል፡፡

 

ግብረ ሰዶማዊያን የክርስትናን እውነት ባለተቀበሉ ማለትም ፤ እግዚአብሔር አንድ ሴት ለአንድ ወንድ አድርጎ ሰራት የሚለውን እውነት በማይቀበሉ ሰዎች የሚዘወትር የሕይወት ስልት ነው፡፡ በመሆኑም ቤተክርስቲያን የትኛውንም ተጽዕኖ (ቀጥተኛ ወይ ኢ-ቀጥተኛ) ለማድረግ ከመጣርዋ በፊት ይህን እውነት እንዲቀበሉ ማስተማርና መጸለይ እንጂ ፤ መቋወም ብቻ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ትግላችን ሊሆን የሚገባው የክርስትናን መሰረታዊ ትምህርት ሰዎች እንዲቀበሉ ማሰተማር ሊሆን ይገባል ፤ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ አስተሳሰባችንና እምነታችንን በሌሎች ላይ መጫን የክርስቶስን የፍቅር ትምህረትና የፍቅር መንግስትን  የሚቃረን ነው ፡፡

 

የዚህ ትምህረት ተቃራኒ አስተምህሮ በሕይወትና በድርጊት ሊገለጡ የሚችሉ ነገሮችን በጥያቄ መልክ ማስቀመጥ ነገሬን የሚገልጠ ይመስለኛል፤ ለምሳሌ ያህል ባነሳ ፡-

  • ጋብቻ መልካም ነው መኝታውም ቅዱስ ነው፡፡ እግዚአብሔር ወንድና ሴት በጋብቻ ይጣመሩ ዘንድ ስጦታ አድርጎ ቅዱስ ጋብቻን ሰጣቸው ብለሕ የምታምን ከሆነና ክርስቶስ ኢየሱስ አንደግል አዳኛቸው አድርገው ያልተቀበሉ ፣ የእግዚአብሔርን ህልውና የማይቀበሉ ፣ በስመ ክርስትና የሚጠሩ ነገር ግን ቅዱስ ቃሉን የካዱ ሰዎች እኔ የማምነውን ማመን አለባቸው የሚለው ሙግት ምድራዊ መንግስት እንዲያስፈጽምልህ የምትተጋ ከሆነ  ፤ ይህ በእውኑ ክርስቲያናዊ ነውን ?
  • ክርስትናን እንደ አንድና ብቸኛ ትምህረት ያልተቀበሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች
    • ከጋብቻ በፊት ይታቀቡ
    • ግድፈት አልባ ንግግር ይኑራችሁ
    • አደንዛዥ እጽ አትጠቀሙ
    • በትዳር ላይ አትወስልቱ
    • ከአንድ በላይ የትዳር አጋር ሃጢኣት ነው
    • ክርስቲያናዊ መንግስትና ሕገመንግስት ይኑር

 

አሁን አንድ ጥያቄን ላንሳ ፡ የመብት - የክርስቲያናዊ መብት ሙገታ ከሆነ ይዘን የምንነሳው ይህ የፖለቲካ ጥያቄና በቀዳሚነትም ክርስቲያናዊ ስነምግባርን በኃይልና በተጽዕኖ በሌሎች ላይ ከመጫን ተለይቶ የሚታይ አይመስለኝም፡፡ ግን ለምን?  እኔ በግሌ በክርስቶስ አዳኝነትና በጤናማ ክርስቲያናዊ ኑሮና የህይወት ስልት አምናለሁ፡፡  ይህንኑም አስተምራለሁ ፣ እመክራለሁ፣ እስብካለሁ፡፡

 

አምባገነናዊ መንግስት የግሉን  አመለካከትና ፍላጎት ፣ የሕዝብን ይሁንታ ያለገኘና ሕዝብን የማይወክልን ሃሳብ በዜጎች ላይ በመጫን ይታወቃል ፤ በተመሳሳይ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ነን ባዮችም የዜጎች ችግር በዜጎች መፍትሄ ያገኛል በሚል መናኛ አስተሳሰብና በአብላጫ ድምጽ ና ጩኽት (ይበጃል ወይም አይበጀም ) ሁሉን ይፈቅዳል፡፡

 

እውነተኛዋ የአምላካችን መንግስት ሰዎች የመረጡትን እስከ ውጤቱ ይቀበሉ! የሚል መርህን ያነገበ መንግስት ነው፡፡ ክርሰቲያኖች የእግዚአብሔርን ቃልና እውነት በግዜውም አለግዜውም ከመስበክና ከማስተማር ውጭ፤ ከመንግስቱ መሰረታዊ ትመህርትና አካሄድ እጅግ የራቀ የምንለውን እንዲያው በደፈናዉ ደግፉኝ፣ ምረጡኝ ማለት አይመስለኝም፡፡

 

3. ቤተክርስቲያን ከጋብቻ ውጭ የሆነ  ወሲብን ትቃወማለች

ግብረ ሰዶማዊነት ሃጢኣት ነው  እንደምንለው ሁሉ ከጋብቻ ውጭ የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግኑኝነትም ሃጢኣት ነው፡፡ የሃጢኣት ትልቅና ትንሽ የለውም ለማለት ብቻ ሳይሆን ፤ የትኛውም ሃጢኣት በደል መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ዳግም ተወልደናል በምንለው በእኛው ማህበረሰብ ውስጥ ሳይቀር እንደዚህ አይነት ነውር በየዕለቱ የምንሰማው የገበናችን ምስጢር ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ  ሰዶማዊነት በድብቅም ቢሆን ላለመኖሩ እርግጠኖች መሆን ይከብደናል፡፡ በየትኛውም መመዘኛና መስፈረት ሃጢኣት ፣ ሃጢኣት ከመሆን አይቀየርም፡፡

 

ቤተክርስቲያን ዓለማዊነትን የደገፈችበትና ፤ ለዓለማዊነት በሯን እንድትከፍት ያልተሞከረ ጥረት  እንዳልነበረ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ በአንጻሩም ተጋርጦባት የነበረወን ችግር አባቶች በአንድ የእምነት ቃልና እስከ ሞት በሚደርስ ተጋድሎ እንዴት እንደ ቀለበሱት የሚያወሳው ሕያው ምስክርነታቸው በእኛ ዘንድ ይሰማል፡፡ ዛሬም ቢሆን በተመሳሳይ ይሁን በተቃራኒ ጾታ መካከል የሚደረግ ከጋብቻ ውጭ የሆነ ወሲብ ሃጢኣት እንደሆነ ልታስተምር ይገባታል፡፡ ቃሉ እንደሚያስተምረን በባልና ሚስት መካከል የሚደረግ እንጂ በባልና ባል ወይም በባልና ሚስት መካከል የሚደረግ አለመሆኑን የዘመኑ የስብከት ርዕስ ሊሆን የተገባ ነው፡፡

 

4. ጥንታዊቷ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ከመንግስት ምሪትና አቅጣጫን አትቀበልም

መንግስታት በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች እንደ ተማርነው ከዳር ለማድረስ የሚጥሩት ዝናቸውና ጀግንነታቸውን ሊያወጣ በሚችል የጀብድ ሥራ ላይ ነው፡፡ ይህ ካለተሳካላቸው ሰፊው ሕዝብ ብለው በሚጠሩት ሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነታቸውን ለማረጋገጥ ሽር ጉድ ማለት ይሆናል፤ እንደ ሶስተኛ አማራጭ መንግስታት በጀብድ ሥራቸው ልህቀታቸውን ማሳየትና ተወዳጅነትን ማፍራት የማችሉ ከሆነ ተፈሪነትን ይመርጣሉ፡፡

  

እንግዲህ እነዚህ መንግስታት የሚሰጡን የትኛውም አመራርና አቅጣጫ ሊመነጭ የሚችለው መንግስታቱ ትርፍ ያስገኝልኛል ብለው ከሚያስቡት የምስረታ ሃሳብ ላይ ይሆናል፡፡ መፈራት አሊያም መወደድ!  ቤተክርስቲያን በመንግስት የሰፊው ሕዝበነት ድርሻን ያገኘች እንደሆነ ፤ መንግስት በእርሷ በኩል ሊያተርፍ የሚፈልገውን ያህል የፍቅር ወይም የፍርሃት ትርፍ ማተረፉን ማረጋገጥ አለበት፡፡ አመራሩም መሰረት የሚያደርገው ከትርፍ አንጻር መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

  

ጌታችን በምድር ቆይታው ላይ  አንድም ግዜ የምድር መንግስት ሥርዓት ይቀየር ወይም እንትን የሚባለው ፖሊስን እቃወማለሁ ብሎ ከሙግት ውስጥ አልገባም፡፡ ይልቁንም ሁሉን የምትገዛ መንግስት መጥታለች ብሎ አገልግሎቱን እንደጀመረ አንብበናል፡፡ መንግስቱም ከዚህ ዓለም እንዳልሆነች አስረግጦ ሰብኳል፡፡  በሌላ ንጽጽር ፤  ጌታ የምድር ነገስታትና መሪዎች ሕይወት ሲቀየር በእነርሱም አልፎ ሲሰራ አንብበናል፡፡

 

ቅዱስ ጳውሎስ በተቀበለው ጌታና ካመነበት ትምሕረት የተነሳ በተደጋጋሚ ስደትና መከራ መቀበሉን በመጨረሻም በመንግስት ተገድሎ እንደሞተ እናውቃለን፡፡ ጳውሎስ በአንዳች ሃይልና ተቃውሞ መንግስት እንዲፈታው ከመጠየቅ ይልቅ ከእስር ቤት ሆኖ ሰዎችን ሁሉ ከጨለማ ማውጣት የሚችለውን የሰማይን መንግስት ወንጌል መጻፍን መርጧል፡፡  ከመንግስት ምሪትናና አቅጣጫን ከመቀበል ይልቅ ከሰማይ መንግስት ጋር መስማማትን የእምነት አባቶቻችን አስተምረውናል፡፡

 

አሁን እንደምናየውና ፣ ከምናየው ተነስተን ስለ መጪው የቤተክርስቲያን ዘመናት ትንቢትን ብንናገር መጪው ዘመን ለታማኝ ቅዱሳንና ለክርስቶስ ቤተክርስቲያን አስጨናቂ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ከመቸውም ግዜ በበለጠ ሁለገብ መንግስታት እየተፈጠሩና በስም እንበለ ዲሞክራሲ የብዘሃን ድምጽ አባዜ ፤ የቅዱሳን የማምለክና የመስበክ ፣ ትምህርታቸውን የማስተማርና የማስፋፋት መብት በመቻቻልና በአክራሪነት ጥርነፋ ስር ሊወደቁ እንደተቃረቡ አስተውላለሁ፡፡

  

በተለየም ቀለም ጠለቅ አማኞች በቤተክርስቲያን ውስጥ ከመብዛታችንና ለቅዱሳት መጽሃፍት ያለን ግንዛቤ አናሳ ከመሆኑ አኳያ የሰብዓዊ መብትና ግለሰባዊነት ከተጸናወተው ኑሯችን ጋር ተዳምሮ ሌላኛው የቤተክርስቲያን ስጋት ሆኖ ይታኛል፡፡ ቀለም ጠለቄዎች ለመደበኛው የሕይወት አሰላለፍና የማሕበረሰብ አወቃቀር ምቹ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ‹‹የምን አገባኝ›› አመለካከትን ለማዳበር የሚያስችል ግለሰባዊነትን እንዲያዳብሩ በመደረጋቸውም ጭምር ነው፡፡

  

ቀለም ጠለቅ ፖለቲካ ዘመንተኛ ከመሆኑም በላይ ፤ መንግስታትም በቀላሉ ሊደለሉበት የሚችሉት አይነት አስተሳሰቦችንም ያከለ ነው፡፡ ዲሞክራሲ በድህረ ዘመናዊት ዓለም ውስጥ በቀለም ጠለቅ ግለሰቦችና አስተሳሰብ የምትነዳ ትንሽ መኪናን ይመስላል፡፡ ቀለም ጠለቄዎች ከቤንዚን ሞተር ወደ ኤታኖሎል  ሞተር ባደረጉት የሽግግር የሙከራ ሂደት፣ ቤተ ሙከራዋ ይችው ትንሽ መኪና በመሆኖ ኑሮዋ የፍዳ እንዲሆን የተፈረደባት ትመስላለች፡፡ የቀለም ጠለቆች አመለካከትና አስተሳሰብ በተቀየረ ቁጥር ቤተ ሙከራው ያው ሕዝብ መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ መንግስታትም ይህንኑ የቀለም ጠለቆች ምክርና አስተሳሰብ እያቀያየሩ ሕዝባቸው እንዲወዳቸው ካለሆነም እንዲፈራቸው ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡ ታዲያ የዘመኑዋ ቤተክርስቲያን ምሪትና አቅጣጫን ከመንግስት ልትወስድ ይገባታልን ?

 

5. ቤተክርስቲያን ከግብረ ሰዶማዊያኑ (ከ ቀላጮች ፣ ወነደቃዎች ና ጾታ ከቀየሩ ሰዎች) ጋር ያላት ግኑኝነት ከፈራጅና ተፈራጅ ወደ አፍቃሪና ወደ ክርስቶስ ሕብረት መላሽነት ሊሸጋገር ይገባል፡፡

 

እግዚአብሔር አምላካችን ሁሉንም ይወዳል ፣ ጌታ ሃጢኣተኛውን ይወዳል፡፡ አንዳድ ግዜ አማኝ የሆንን እኛ በሃጢኣትና በሃጢኣተኛው መካከል ያለውን ልዩነት የምንረሳው ይመስለኛል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ስለ አንድ ሃጢኣተኛ ሲል ዘጠና ዘጠኙን በቤት አስቀምጦ አንዱን ፍለጋ እንደሚወጣ አስተምሯል፡፡ የቤተክርስቲያንም ዋነኛ ስራ የጠፉትን መፈለግ እንጂ በጠፉት ላይ መፍረድ አይደለም፡፡

 

ግብረ-ሰዶማዊነት ሃጢኣት ነው፡፡ ይህ ምንም ድርድር የሌለው ነው፡፡ የጌታ የኢየሱስ ደም ከሃጢኣት ሁሉ ያነጻል ፤ ግብረሰዶማዊነትም  እንኳን ቢሆን፡፡ ስለ ወንጌል የምናደረገው ቀናዊነትና ተጋድሎ እውነትን መሰረት ያደረገና የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ሃሳብ ያማከለ ሊሆን ይገባል፡፡ ወንጌል የምስራች ነው፡፡ ይህ የምስራች ከጨለማ ወደ ብርሃን ተሸጋግረሃል የሚል በመሆኑ ፤ እኛም ለነዚህ የጠፉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ልናካፍላቸው የሚገባን ይህንኑ ነው፡፡

 

እኛም ብንሆነ የዳነው በእርሱ ቸርነትና ቤዛነት መሆኑን መዘንጋት ፤ የዳንበትን ትምህርት እንደ መቃወም መቆጠር ይኖርበታል፡፡ ሌሎችንም የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ከዓለማዊነትና ከዚህ ዓለም አባዜ አላቆ ማኖር መቻሉን ልናስተምራቸው የሚገባ ሃቅ ነው ፤ ለእኛም እንደ ቤተክርስቲያን ልጅነታችን የዘወትር ትውስታችን መሆን ሊሆን ግድ ነው፡፡

ወንጌል ሰባኪነት ፣ በኢየሱስ የተሰራውን የድነት ሥራ ማስተማርና እንዲያምኑ መርዳት እነጂ ፤ ግለሰቦቹ ያሉበትን ሁኔታ እንደ ማነጻጸሪያ በማንሳት በእነርሱ ላይ መፍረድ አለመሆኑን ከጌታ ኢየሱስ ሕይወት ተምረናል፡፡ እርሱ በሰራው ስራ ፤ ሃጢኣተኛው በሚያጸድቅ ባመነበት በአምላኩ ፊት ለአብርሃም እንደተባለለት እኛም ብንሆን የዳንበት መዳን ከራሳችን ባለመሆኑ ፤ የሰራነውን ሳይሆን የተሰራልን በማመን ያገኘነውን ሕይወት ላልዳኑት በየዋሕነትና በብዙ ፍርሃት እንድናከፍላቸው እመክራለሁ፡፡

 

ማጠቃለያ

የቅዱሳንና የቤተክርስቲያን ተጋድሎ አሁን ካለበት ደረጃ ወደ ከፋ ደረጃ መሸጋገሩ የማይካድ የመጽሃፉ ሃቅ ነው፡፡ እውነት ነው ፤ ከዚህ በኋላ የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ እናውቃለን፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ብዙ ሰዎች በራሳቸው ፍላጎትና መብት ዙሪያ የሚኖሩበት ቀን ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡ እኛ ግን ፡- እውነትን ብቻ በመያዝ ልንኖር ተጠርታናል ፤ ይሕ እውነት ከዘመናት አስቀድሞ ለአባቶች የተሰበከ ይሁን እንጂ ዛሬም በእኛ ዘመን ለጨለመበት ብርሃን ነው፡፡ ግራ ለገባው መረጋጋት ነው፡፡  መንገድ ለጠፋው መንገድ ነው፡፡

 

ከተቀበልነው የአውነት ደረጃ እና የእውነት መንገድ ጋር ስናስተያየው  የተሸከምነው  ሃላፊነት አሁን ካለን ለዘብተኝት አንጻር ከፍርድ ማምለጥ በማንችልበት እርምጃ ውስጥ ነን ብዬ አምናለሁ፡፡ ብዙዎች የሕይወትን መንገድ በሚናፍቁበት በዚህ ዘመን እንደ እነ ሃጌ ዘመን የእግዚአብሔርን ስራ ሳይሆን የራሳችንን ቤት እየገነባን እንገኛለን፡፡ መድረኮቻችንም ቢጠየቁ ይህን እውነት አያብሉም፡፡ ትበላለህ፣ ትጠጣለህ ፤ ትከብራለህ ፣ ከፍ ትላለለህ… እረ ምኑ ቅጡ! ክርሰቶስ የሞተለት ሰው ተረስቶ ፤ ወንጌል ሰባኪ ተብዬው በየመድረኩ ኑሮውን ያበጃል፤ መከናወኑን ይመሰክራል፡፡

 

ቅድሰት ቤተክርስቲያንና የቤተክርሰቲያኝ ልጆች ወደ ጌታ ጎተራ ብዙዎችን ልንጠራ የሚገባን ሰዓት ከመቸውም ጊዜ ይልቅ አሁን ነው፡፡ ከዳር ቆመን አፋችንን በአፍረትና በጊዜኣዊ ፍላጎታችን አፍነን ፤ ከመንግስቱ ወንጌል ይልቅ ለጊዜው የሚያባብለንን ጊዜያዊ ስሜታችንን ወግድ ብለን ፤ የምስራቹን ለማወጅ ፣ የድል አድራጊውን ወንጌል ገድል በማሰቀጠል ወደ ድል አድራጊነት የምንሸጋገርበት የወንጌል ዘመን አሁን ነው፡፡ ወንጌል የሰዶማዊያኑ  ብቸኛው የነጻነት በር ነው!

Read 7429 times Last modified on Wednesday, 08 July 2015 12:03
Yoseph Lemma

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Nahu's Corner

 

 

 

.

Right Now

We have 226 guests and no members online

About Us

Semayawi Thought is an online magazine published in Amharic and English, focused on contents to spiritual and personal growth.